ጀርመን በመጪው እሁድ በምታካሂደው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለ4ተኛ ጊዜ የሚወዳደሩት መርሔ መንግስት አንጌላ ሜርክል የማሽነፍ እድላቸው ሰፊ ነው ተባለ
ቻይና ለሰሜን ኮሪያ ተማሪዎች ሰጥታ የነበረውን ነፃ የትምህርት እድል ሰረዘች፡፡ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊያጠኑ የመጡትን ከሀገሬ ሂዱልኝ ብላ መለሰች፡፡
72ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳና እየተወያየ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው መወያያ መድረክ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ደመቅ ብሎና አከራካሪ ሆኖ እንደጀመረ እየተነገረ ይገኛል፡፡193 አባል ሀገራት ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ኒዮርክ በሚገኘው ዘመናዊ አዳራሹ በማደረግ ላይ ያለውን ስብሰባ ካሳሁን መብራቱ ተመልክቶታል
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ነበር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርጅቱን ወቅሰውና አሰራሩ መታረም እንዳለበት በመጠቆም ባማደረግ ነበር ስብሰባውን የጀመሩት በዚህም ብዙዎችን አነጋገራል ፡፡ ትራምፕ በዚህ መድረክ ላይ ስለ ድህነት፣ስለ ስደተኞችና ስለ ሰሜን ኮሪያ በሰፊው አውርተዋል፡፡
በተለይ ሰሜን ኮሪያ አደርሳለሁ ያሉት ጥቃት ዛቻና በሰሜን ኮሪያ ላይ እጥላለሁ ያሉት ማዕቀብ በሰፊው አስተችቷቸዋል፡፡ ትራምፕ ከዚህ በኋላ ትዕግስታችን አልቋል የሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን እስከመጨረሻው አመድ እናደርጋታለን ሲሉ ለሀገራቱ መሪዎች ገልጸዋል፡፡
ወደ አሜሪካ ያለማቋረጥ የሚጎርፉትን ስደተኞችንም አገሮች እንዲይዙላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሳቸው ንግግር በኋላ ወደ መድረኩ እየወጡ ከሚናገሩት መሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ የትራምፕ ነቃፊ የነበሩ ሲሆን ያቀረቡትን ንግግርም ቦታው እዚህ አይደልም ብለዋቸዋል፡፡
ለምሳሌም የኢራኑ መሪና የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘንድሮው የውይይት መድረክ ለየት ያለና ወደፊት ሊሰራው ያቀደውን ፕሮግራም የሚያስተዋውቅበት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ስደተኞች በሀገራቸው ደልቷቸው እንዲኖሩ መሪዎች ማድረግ ያለባቸው ነጥቦችን አንስቶ ይወያይበታል፤አለማቀፍ ሽብርተኝነትን በተመለከተም የዘር ግጭትንና የእርስ በርስ ጦርነትን እያወግዘ ችግሩን ከነመፍትሔው ይዳስሳል ፡፡ የአየር ንብረት መለዋወጥንም ዋና ጉዳዩ አድርጎ እየመከረ ይገኛል፡፡
እንደዋይት ሃውስ መረጃ ከሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ የተገኙ የተለያዩ የሀገር መሪዎችን በጎን እያገኙ መወያየታቸው ተመልክትዋል